ስለ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ስልጣን ምን ያውቃሉ?

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን የመነጨው ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 80 ንዑስ አንቀጽ 3(ሀ) ነው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ የህገ-መንግስት አንቀፅ 80 (1)፤(4)፤(6)እና (8) ስንመለከት በፌዴራል ሆነ በክልል ፍርድ ቤቶች በሶስት የተዋረድ እርከን ማለትም በመጀመሪያ ደረጃ፤ በከፍተኛ እና በጠቅላይ ፍርድ ቤቶች እንደሚዋቀሩ ያስቀምጣል፡፡
ይህንን የህገመንግስት ድንጋጌ መሰረት በማድረግ ሰበር አራተኛው ደረጃ ፍርድ ቤት ነውን? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በአንቀፅ 80 (3) ሀ እና ለ የተጠቀሰው እንዲሁም በዚህ አንቀፅ ላይ በህገ-መንግስት ጉባኤ የተደረገው ውይይት ቃለ ጉባኤ ሰበር የተለየ ፍርድ ቤት ሳይሆን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የሚቋቋም ልዩ ችሎት ነው በማለት ያብራራል፡፡
ህገ-መንግስቱን ተከትሎ የወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 10 የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለባቸውን፡-
የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች፤
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች
የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት ወይም በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች፤
እንዲሁም በህገመንግስቱ በማናቸውም ፍርድ ቤቶች የተሰጡትን የመጨረሻ ውሳኔዎች የማየት ስልጣን የተሰጠው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባና የድሬደዋ ከተማ ፍርድ ቤቶች በሰጡት የመጨረሻ ውሳኔ እና ወታደራዊ ፍርድ ቤት በይግባኝ የሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ በሰበር የማየት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡
በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀፅ 21(2)(ሐ) መሰረት አንድ ጉዳይ በሰበር ሲታይ ከአምስት ያላነሱ ዳኞች ሊሰየሙ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎት የስነስርአት አካሄድ በተመለከተ አቤቱታ አቅራቢ በማመልከቻው ላይ ተፈፀመ የሚለውን የህግ ስህተት በዝርዝር ውሳኔ በተሰጠ በ 90 ቀናት ውስጥ ፅፎ ከስር ፍርድ ቤት ውሳኔዎች ጋር አያይዞ ማቅረብ እንዳለበት፤ የሰበር አቤቱታ ሲቀርብ በቅድሚያ ሶስት ዳኞች የተሰየሙበት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት ጉዳዩ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በሚል ሲያቀርቡት ብቻ እንደሚመለከት በአዋጁ ላይ ተቀምጧል (አንቀጽ 22 (1-4)፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 454/97 መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የህግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌዴራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት እንደሚኖረው ተደንግጓል፡፡

ከረፖርተር ጋዜጣ የተወሰደ

  • Posted from WordPress for Android

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ