Category Archives: BLOG

እነ አቶ መላኩ ፈንታ ከተከሰሱበት የክስ መዝገቦች በአንደኛው ላይ ዛሬ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እነ አቶ መላኩ ፈንታ ከተከሰሱበት የክስ መዝገቦች በአንደኛው ላይ ዛሬ ብይን ተሰጠ። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጀል ችሎት ዛሬ ብይን የሰጠው ስራን አላግባብ መምራት፣ በስልጣን አላግባብ በመጠቀም፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት በማንቀሳቀስ እና ህጋዊ አድርጎ በማቅረብ በሚሉት ክሶች ላይ ነው
የፌደራል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በቀድሞ የገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለሰልጣን በተለያየ ሀላፊነት ላይ በነበሩ ከተሳሾች ላይ 17 ክሶችን መመስረቱ ይታወሳል።
ስራን አላግባብ መምራት፣ በስልጣን አላግባብ በመጠቀም፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት በማንቀሳቀስና ህጋዊ አድርጎ በማቅረብ በሚል ነው አቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ክስ የመሰረተው።
በአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ አቶ መላኩ ፈንታ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር፣ 2ኛ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ የባለስልጣኑ የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ 3ኛ አቶ በላቸው በየነ የኦዲት ዳይሬክተር፣ 4ኛ አቶ ማሞ አብዲ የታክስ አማካሪ እንዲሁም የቴክኒክ ኮሚቴ አባል እና ጸሃፊ ናቸው።
ከ5ኛ እስከ 11ኛ በመዝገቡ የተጠቀሱት ተከሳሾች ክሳቸው በአቃቤ ህግ የተቋረጠ ሲሆን፥ ከ12ኛ እስከ 17ኛ ባሉት ተከሳሾች ላይ ደግሞ ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት ብይን ሰጥቷል።
ከ1ኛ እስከ 4ኛ ባሉት ተከሳሾች ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ 1ኛ ተከሳሽ አቶ መላኩ ፈንታ በአዋጆች ለአቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ የተሰጠውን ስልጣን ተግባራት የሚሽር እና በአዋጆቹ መሰረት የቀረቡትን አቤቱታዎች እንደገና መከለስ የሚያስችል ህገወጥ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም እና መመሪያ በማውጣት ሀዋስ አግሮ ቢዝነስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለተባለ ድርጅት የቅሬታ አቀራረቡን በመጣስ ተከሳሹ አቤቱታ እንዲቀየር በማድረግ እና በህገወጥ መንገድ የተቋቋመው ኮሚቴ እንዲያየው በማድረግ መንግስትን 22 ሚሊየን 379 ሺህ 140 ብር አሳጥተዋል ይላል።
2ኛ ተከሳሽ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስም ውሳኔው ተፈጻሚ እንዲሆን ትእዛዝ የሰጡ ሲሆን፥ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች የቴክኒክ ኮሚቴው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።
ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽ ያወጡት መመሪያ አዋጁን የሚቃወም እና ከአዋጁ ጋር የሚጣረስ ነው ያለ ሲሆን፥ በመሆኑም መመሪያው የወጣበትን አግባብ እና የቴክኒክ ኮሚቴ የተቋቋመበት አግባብ ላይ ላይ የቀረበባቸውን ክስ 1ኛ ተከሳሽ እና በክሱ የተጠቀሱት ሌሎች ተከሳሾች ሊከላከሉ ይገባል ብሏል።
በ2ኛው ክስም 1ኛ ተከሳሽ ያማቶ ኢትዮጵያ ለተባለ ድርጅት ከ1996 እስክ 2001 ዓ.ም ድረስ ያለው የተጨማሪ እሴት ታክስ የንግድ ስራ ገቢ ኦዲት ተደርጎ በድምሩ 48 ሚሊየን 444 ሺህ ብር ቢወሰንባቸውም የግለሰቡን አቤቱታ በመቀበል እና በኮሚቴው እንዲታይ በማድረግ ወደ 34 ሚሊየን ብር ዝቅ እንዲል አድርገዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ወስኗል።
3ኛው ክስ በ2ኛው ተከሳሽ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ላይ ሲሆን፥ ሼባ ስቲል ማይልስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ኩባንያ ከ1996 እስከ 1997 ዓ.ም ባለው ጊዜ የንግድ ትርፍ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ 1 ሚሊየን 487 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ቢወሰንባቸውም ተከሳሹ ውሳኔው እንደገና እንዲታይ በማዘዝ የመንግስት ግብር እንዳይሰበሰብ አድርገዋል ይላል።
ይሁንና በ2ኛ ተከሳሽ ላይ ከቀረበው የሰነድ ማስረጃ አንጻር ተከሳሹ ድርጊቱን መፈጸማቸውን ስለማያሳይ ሊከሰሱ አይገባም ሲል ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል።
4ኛ ክስ በ2ኛ እና በ12 ተከሳሾች ላይ ሲሆን፥ ይህም አልማ ፋርምስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከሀምሌ 1996 እስክ 2000 ዓ.ም የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የንግድ ትርፍ 7 ሚሊየን 966 ሺህ 740 ብር እንዲከፍል ቢወሰንም ተከሳሾቹ ወደ 480 ሺህ ብር ዝቅ እንዲል አድርገዋል።
በዚሁ ክስ ለሪፍት ቫሊ ሆቴል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የንግድ ትርፍ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ዝቅ አድርገው እንዲከፍሉ በማድረጋቸው ተከሰዋል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔው ለባለስልጣኑ አቤቱታ አቅራቢ ቀርቦ መወሰን ሲገባው በኮሚቴ መወሰን አግባብ አይደለም ያለ ሲሆን፥ 2ኛ ተከሳሽ ይከላከሉ በማለት፤ 12ኛ ተከሳሽ ግን ታዞ ኦዲት ያደረገ እና የተሰጠው ውሳኔ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ያደረገ በመሆኑ መከላከል አይገባውም ብሏል።
6ኛ ክስ በ2ኛ ተከሳሽ ላይ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ሊከላከሉ እይገባም ብሏል።
7ኛ ክስ በ1ኛ፣ በ2ኛ እና በ13ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን፥ ተከሳሾቹ ክሱን እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
በ9ኛ እና በ10ኛ ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ በክሱ ከተጠቀሰው ከ3 ሚሊየን ብር ውስጥ በ791 ሺህ 115 ብር ላይ ይከላለኩ የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷል።
በ11ኛ ክስ 1ኛ ተከሳሽ አቶ መላኩ ፈንታ የመንግስት ተሽከርካሪ ያለአግባብ በጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል በሚለው ክስ እንዲከላለከሉ የተባለ ሲሆን፥ በ12ኛ ክስ 12 ተከሳሾች ይከላከሉ እንዲሁም በ13ኛ ክስ 13ኛ ተከሳሽ ሊከላከሉ አይገባም ተብሏል።
በ15ኛ ክስ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያሉ ተከሳሾች ሳይከላከሉ በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን ተሰጥቷል።
16ኛ ክስ የተሰረዘ ሲሆን፥ በ17ኛ ክስ 4ኛ ተከሳሽ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጀል ችሎት የመከላከያ ምስክር ለማስማት እንዲረዳቸውና መግለጫ ለማቅረብ ችሎቱ ለሰኔ 15 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

image

በብስራት መለሰ

– See more at: http://www.fanabc.com/index.php/news/item/15629-%E1%8A%A5%E1%8A%90-%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%88%98%E1%88%8B%E1%8A%A9-%E1%8D%88%E1%8A%95%E1%89%B3-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%8A%A8%E1%88%B0%E1%88%B1%E1%89%A0%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%8A%AD%E1%88%B5-%E1%88%98%E1%8B%9D%E1%8C%88%E1%89%A6%E1%89%BD-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B0%E1%8A%9B%E1%8B%8D-%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%8B%9B%E1%88%AC-%E1%89%A5%E1%8B%AD%E1%8A%95-%E1%89%B0%E1%88%B0%E1%8C%A0%E1%8A%A5%E1%8A%90-%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%88%98%E1%88%8B%E1%8A%A9-%E1%8D%88%E1%8A%95%E1%89%B3-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%8A%A8%E1%88%B0%E1%88%B1%E1%89%A0%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%8A%AD%E1%88%B5-%E1%88%98%E1%8B%9D%E1%8C%88%E1%89%A6%E1%89%BD-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B0%E1%8A%9B%E1%8B%8D-%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%8B%9B%E1%88%AC-%E1%89%A5%E1%8B%AD%E1%8A%95-%E1%89%B0%E1%88%B0%E1%8C%A0.html#sthash.jPsTZ01V.dpuf